ሜጋ ፒክስል ለፎቶ ጥራት አያስፈልግም አሉ፡ እውነት | ሀሰት

ሜጋ ፒክስል ለፎቶ ጥራት አያስፈልግም አሉ፡ እውነት | ሀሰት


Amharic

መግቢያ

የiPhone 14 ካሜራ ስንት ሜጋ ፒክስል ይመስላቿል? መቼም ፎቶው ኖርማሉን ካሜራ ይመስላል እየተባለ አይደል የሚወራው። 64? ወይ 48? በቃ አነሰ ከተባለ ከ30 በላይ አይሆንም? አይሆንም! እውነታው የiPhone 14 ካሜራ 12 MP ብቻ መሆኑ ነው።

ቆይ ቆይ እንዴ እዚ በአስራ ምናምን ሺ ብር የሚገዛ Tecno ስልክ እራሱ 16 MP አይደል እንዴ (Tecno ተራ ኩባኒያ ሆኖ ሳይሆን ዝቅተኛ ዋጋ እና አቅም ያላቸው ስልኮች በብዛት ስለሚያመርት ነው ለንፅፅር የመረጥኩት) እንዴት ከiPhone ይበልጣል? ከተበለ፣ መልስ የሚሆነው ለስልክ ካሜራ ጥራት ከMP ቁጥር ባሻገር ብዙ አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ ነገሮች መኖራቸው ነው። መጀመሪያ ግን እስኪ ሜጋ ፒክስል እራሱ ምንድነው? እንዴትስ ነው የሚቆጠረው የሚለውን ቃኘት እናድርግ።

ሜጋ ፒክስል ምንድነው

ሜጋ ፒክስል ቃል በቃል ትርጉሙ 1 ሚሊዮን ፒክስሎች ማለት ሲሆን ማንኛውም ምስልም ሆነ ቪዲዮ ስንመለከት ከቀይ፣ አረንጓዴ እና ሰማያዊ ቅልቅል ከለሮች አንዱን በመያዝ በሺዎች የሚቆጠሩ ነጥቦች በህብረት የሰሩትን ጥንቅር ነው እየተመለከትን ያለነው። ከነዚህ ነጥቦች አንድ ከለር ብቻ መያዝ የምትችለው አንዷ ነጥብ አንድ ፒክስል ትባላለች። ለምሳሌ አንድ 1080p ወይም FullHD ቴሌቪዥን በውስጡ 1080 ሲባዛ በ1920 ወይም 2,073,600 ፒክስሎች አሉት።

pixels-large.jpg የቲቪ ስክሪን ፒክስሎች በቀረቤታ ሲታዩ የሚያሳዩት አቀማመጥ

ይም ማለት አንድ 12 MP የሆነ ካሜራ 12 ሚሊየን ፒክስሎችን በአንድ ቅፅበት መቅረፅ ይችላል። ያ የሚሆነው ታዲያ ቅድም ያነሳናቸው ሌሎቹም አካላት አብረው በዚው ፍጥነት መንቀሳቀስ የሚችሉ ሲሆኑ ብቻ ነው። ለመሆኑ እነማን ናቸው? ለአንድ ስልክ ካሜራ ጥራት ትላልቅ ሚና የሚጫወቱት ክፍሎች መካከል ሁለቱን አበይት ክፍሎች እንመልከት

ተፅዕኖ ፈጣሪዎች

1. የፒክስል መጠን

ሜጋ ፒክስል የፒክስሎች ስብስብ ነው ካልን የአንዱ ፒክስል መጠን ምን ያክል ነው የሚለውም አብሮ መነሳት ይኖርበታል። ብዙ ጊዜ ስማርት ስልኮች እንደውም ከፍ ያለ MP ሲኖራቸው የእያንዳንዱ ፒክስል መጠን እያነሰ ይሄዳል። ትናንሽ ፒክስሎች ደግሞ ብርሀንን የማስገባት አቅማቸው ከመጠናቸው ጋር ይቀንሳል።

የትኛውም ምስል ጥራት እንዲኖረው እና ከNoise የፀዳ እንዲሆን በቂ የሆነ የብርሀን መጠን ሊኖረው ይገባል። ይህ ማለት ኩባኒያዎች ለስልኮቻቸው ካሜራ ሲመርጡ ሜጋ ፒክስሉን እናብዛው ካሉ በአንድ በኩል የምስሉን ጥራት እየጨመሩ በሌላ በኩል ደግሞ እነዛ ምስሎች ላይ አላስፈላጊ የሆነ Noise እየጨመሩ ይሄዳሉ ማለት ነው። ብዙ ጊዜ የNoise ውጤት በባህሪው ምሽታማ የሆኑ እና ጨለማ ክፍሎችን የያዙ ምስሎች ላይ የተጋነነ ይሆናል።

Noise መጠኑ የበዛ እና የተስተካከሉ ተመሳሳይ ምስሎች (ለማሳየት ያክል) Noise መጠኑ የበዛ እና የተስተካከሉ ተመሳሳይ ምስሎች (ለማሳየት ያክል)

2. ሴንሰር

ሁሉም ካሜራዎች ከጀምራቸው Optical የሆነን በሌንስ በኩል የሚመጣውን ምስል ወደ ዲጂታል ዳታ የሚቀይር ሴንሰር አላቸው። ሴንሰሮች ታዲያ እንደሌሎቹ ክፍሎች በተለያዩ መጠን እና ጥራት ተዘጋጅተው ይቀርባሉ። ከፍተኛ ጥራት ያላቸው እንዲሁም መጠናቸውም ከፍ ያለ በሆኑ ቁጥር የሚሰጡትም ምስል በዛው ልክ የተሻለ ይሆናል።

አሁን ላይ ትልቅ የሚባለው የስልክ ሴንሰር እስከ 1 ኢንች የሚደርስ እና እስካሁን Xiaomi, Vivo እና Sony ስልኮች ላይ በተግባር የታየ ነው። እነዚህ እና ሌሎች የካሜራ ክፍሎች ተደምረው ከሚያመጡት ምስል ላይ ደግሞ የስልኩ Image signal processor (ISP) የራሱን ኤዲቲንግ ጨምሮ አቀናብሮ እና አሽሞንሙኖ የሚያቀርበውን ምስል ነው እኛ ተጠቃሚዎች የምናየው። ለዚህ ነው ስልክ ላይ የካሜራውን ጥራት በሜጋ ፒክስል ብቻ አይቶ ለመወሰን እጅግ አዳጋች ነው የምለው። ይህ ማለት ግን ሜጋ ፒክስል ምንም ጥቅም የለውም ማለት አይደለም! ምክኒያቱም ለምሳሌ አሁን ላይ የፎቶ ንጉሳን ሊባሉ ከሚችሉ ስልኮች አንዱ የሆነው Samsung Galaxy S23 Ultra ባለ 200MP ካሜራ ነው።

እና ምን ተሻለ

ጥቆማዬን ከማስቀመጤ በፊት አንድ ልጠቅስላቹ የምፈልገው ነገር ቢኖር MKBHD የተሰኘው እውቅ ዩቲውበር በየአመቱ የጊዜውን አሪፍ የሚባሉ ስልኮች በመውሰድ በካሜራ ጥራት የሚያደርገውን ውድድር ነው። ውድድሩ የሚካሄደው ኦልናይን ሁሉም እንዲሳተፍ ክፍት በሆነ መልኩ ሲሆን ለየት የሚያደርገው ምርጫው ላይ የሚሳተፉ ሰዎች የሚወዱትን ፎቶዎች ሲመርጡ በየትኛው ስልክ እንደተነሳ ሳያውቁ ነው። ይህ በመሰረቱ ምርጫቸው አድሎ እንዳይኖረውም ይረዳል። የሚገርመው አሸናፊ ሆነው የሚወጡት ስልኮች አንዳንዴ በዋጋም በቴክኖሎጂም ዝቅ ያሉ ስልኮች ናቸው። ይሄ ለኔ የሚያሳየኝ የስልኮች ፎቶ የማንሳት አቅም በጣም እንደላቀ እና እንዲው በአይናችን ልንለየው የምንችለው ልዩነት በውድ እና ርካሽ ስልኮች መካከል እንኳን ማግኘት አዳጋች የሆነበት ደረጃ ላይ እየደረስን እንዳለን ነው።

ስለዚህ የስልኮችን የካሜራ ጥራት ለማወዳደር ትንሽ አምታች ስለሚሆን በዘርፉ ሙያ ካካበቱ እና አለማቀፍ ተአማኒነት ካላቸው ግለሰቦች እና ተቋማት የሚመጡ ንፅፅሮችን እንዲሁም የተነሱ ፎቶዎችን አይቶ መወሰኑ ሳይሻል አይቀርም። እናንተስ ምን ትላላቹ? እይታዎቻቹን ኮሜንት ላይ ብታስቀምጡ እና ሀሳቡን ብናንሸራሽረው ደስ ይለኛል። ሰላም✌🏼

© 2024 Abdulhafiz Ahmed || haffuz01
Personal Website, Updated October 2023